June 4, 2023

በኢትዮጵያ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል

September 16, 6:39 pm | @EBC


በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በነገው ዕለት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ደህንነት ቀን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን እንዳሉት ኮሮናቫይረስ በተለይ በሽታውን በመከላከል ሥራ ግንባር ቀደም በሆኑት የሕክምና ባለሙያዎች ላይ መጠነ ሰፊ ችግር አስከትሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 1 ነጥበ 3 ሚሊዮን የሚሆኑት የጤናው ሴክተር ሠራተኞች ናቸው። “በኢትዮጵያም ኮቪድ-19 ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 1 ሺህ 311 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከነዚህ መካከል 700 የሚሆኑት አገግመው ወጥተዋል፤ ቀሪዎቹ በሕክምና ተቋማት ይገኛሉ” ብለዋል አቶ ያዕቆብ። ሁለት የሕክምና ባለሙያዎችም ለሞት መዳረጋቸውን ነው ያስታወሱት። ነገ ለሁለተኛ ጊዜ በአገሪቱ የሚከበረው የሕሙማን ደህንነት ቀንም ቫይረሱ የተገኘባቸው ወገኖቻቸውን ሌት ተቀን እያገለገሉ ላሉ ባለሙያዎችና አጋሮቻቸው ክብርና ምስጋናን በመስጠት እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ የጤና ባለሙያዎች በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን ችግር በመፍታትና በማገዝ እንዲሁም ራሳቸውን ከበሽታ ጠብቀው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ በሚያስችሉ ፕሮግራሞች የሚከበር መሆኑንም ነው አቶ ያዕቆብ ያመለከቱት። “በተጨማሪ በዓሉ በቫይረሱ የተጠቁ የሕክምና ባለሙያዎችና ሠራተኞችን በመጠየቅና በማበረታታት ይከበራል” ብለዋል። ህብረተሰቡም የጤና ባለሙያዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሕክምና ቁሶችን ባለማባከንና በማበረታታት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የሕክምና እቃ እቅራቢዎችም በአስቸጋሪ ወቅት ለባለሙያዎቹ የሚያስፈልጉ ቁሶችን በአግባቡ በማቅረብ አብሮነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ኢዜ ዘግቧል።