June 4, 2023
September 11, 8:03 am | @huleAddis
“የቀጣይ ዓመት ውጤታችን የሚወሰነው ለመለወጥ በተዘጋጀነው መጠን ነው” ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር ዐቢይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን ያስተላለፉት የአዲስ ዓመት ዋዜማ በዓል በሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ በድምቀት ሲከበር ነው ። አዲስ ዓመት ምንም ያልተፃፈበት የዘመን መፅሃፍ ነውና ለዚህ ቀን እንኳን አደረሰን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል። ጠቅላይ ሚነስተሩ እስካሁን ባገኘናቸው ድሎች ረክተን አንቀርም ገና ወደ ልዕልና እንመጥቃለን ነው ያሉት ። እንደ ምድር ስበት የሚስቡን ችግሮቻችንን አልፈን ልክ እንደ መንኩራኩር፣ ለዚህ በተዘጋጁ እና በቆረጡ መጣቂዎች እና ባዘጋጀነው የ10 ዓመት ፍኖተ ብልፅግና መንኩራኩርነት ህብረ ብሄራዊነት በተሰኘ ማምጠቂያ ስፍራ ብልፅግና ወደተባለ ደርሰንበት ወደ ማናውቀው የመንፈስ፣ የቁስ እና የኢኮኖሚ ከፍታ እንመጥቃለን ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ በመልዕክታቸው ። 2012 ብዙ ሀዘንና ደስታ የተፈራረቀበት ቢሆንም በዛው ልክ ኢትዮጵያ ጨለማ የማይበግራት የብርሃን ሀገር፣ የብርቱ ህዝብ የፅኑ ዜጋ ሀገር መሆኗ የታየበት እንደነበርም አንስተዋል። ለዚህም የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በስኬት ማጠናቀቋን እንዲሁም የመጀመሪያ ሳታላይት ማምጠቋን በዋናነት ጠቅሰዋል ። ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ማማ ሊያወጣ ራዕይ የሰነቀው ብልፅግና ፓርቲ የነበረውን አሮጌ አስተሳሰብ አስወግዶ የተወለደው በዚህ ዓመት እንደነበረም አስታውሰዋል። አረንጓዴ ሀገር ለመፍጠር 5 ቢሊየን ችግኝ መትከል የተቻለው፣ ምሳሌ የሆኑት የአንድነት ፓርክና እና የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የተጠናቀቁት፣ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም አርሻ ውጤታማ የሆኑት እና ለዓመታት ሲያሽቆለቁል የነበረው የወጪ ንግድ ወደ ዕድገት የመጣው በ2012 መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘርዝረዋል። ከዘመን ወደ ዘመን የምናደርገው ሽግግር ትርጉም እንዲኖረው ካለፈው ዘመን ጋር አሮጌና ጎታች አስተሳሰባችንን ተሰናብተን አዲስ እና ተራማጅ አስተሳሰብን ልንላበስ ይግባል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ። የቀጣይ ዓመት ውጤታችን የሚወሰነው ለመለወጥ በተዘጋጀነው መጠን እንደሆነ ነው የገለፁት። “መጪው ዓመት ስላለፈው የምንቆዝምበት፣ ስላለፈው ቂም ቋጥረን በቀልን የምናስብበት ሳይሆን በይቅርታ እና በእርቅ ሰላምን አውርደን በመተሳሰብና በመደማመጥ ልዩነታችንን አጥብበን ህዝባችንን እና ሀገራችንን በማስቀደም ወደ ልዕልና የምንመጥቅበት እንዲሆን ሀላችሁንም እጋብዛለሁ” ብለዋል።