June 4, 2023
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡኑ መርቆሪዎስ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ላስገኟቸው ስኬቶች ምስጋና አቀረቡ፡፡ ፓትርያርኩ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመገኘት መጪውን አዲስ ዓመት አስመልክተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የእንኳን አደረስዎት ስጦታ አበረክተውላቸዋል፡፡ ፓትርያርኩ በፅሑፍ ባስነበቡት መልዕክታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ በተለይ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ ወደ አንድ በማምጣት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ተይዘው የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሃብቶች ማስመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በአዲሰ አበባ ባስገነባቸው ፓርኮች በተለይ በአንድነት ፓርክ የቤተ ክርስቲያኗ ቅርሶች ለዓለም እንዲተዋወቁ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ''ኦርቶዶክስ ሀገር ናት'' በሚል አማናዊ ምስክርነት ለቤተክርስቲያን ያላቸውን አለኝታነት ማሳየታቸውንም ፓትርያርኩ አስታውሰዋል፡፡ አገር ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት በጥበብ በመምራት ረገድም ጉልህ አስተዋጽዖ ማበርከታቸውንም አቡነ መርቆሪዎስ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ ቤተክርስቲያኗ ጸሎትና ምልጃ እያወጀች አገር ፀንታ እንድትቆም መስራቷንና እየሰራች መሆኗን መስክረዋል፡፡ በቀጣይ የተጀመረው መልካም ሥራ እንዲበዛና አገር እንድትበለጽግ አባቶች በፀሎት እንዲያግዟቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡