March 20, 2023
የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ሱዳንን ከጎርፍ ሊታደጋት እንደሚችል የአገሪቱ የመስኖ ሚኒስቴር ያሲር አባስ ትናንት በዋና በመዲናዋ ካርቱም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ በቅርቡ በሱዳን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደሌለው ነው የመስኖ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ ግንባታ ላይ በተለይም በሙሌትና በአፈፃፀም ጉዳዮች ልዩነቶች እንዳላቸው ተጠቅሷል፡፡ አሁን ሱዳን ያጋጠማት የጎርፍ መጥለቅለቅ ከባለፈው ምዕተ ዓመት ውስጥ እጅግ የከፋው መሆኑን በመግለጽ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አገሪቱን እንዲረዳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአገሪቱ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸውን እና 40 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸው የተገለጸ ሲሆን መንግስት ይህን ተከትሎ ለሶስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን የአናዱሉ ዘገባ ያመለክታል፡፡