February 8, 2023

በሜዲትራኒያን ባሕር በደረሰ የጀልባ አደጋ ሕፃናትን ጨምሮ የ45 ሰዎች ህይወት አለፈ

August 20, 9:41 am | @EBC


በያዝነው ሳምንት ውስጥ በሊቢያ ዳርቻ በተከሰተው የጀልባ አደጋ አምስት ሕፃናትን ጨምሮ ቢያንስ የ45 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተመድ አስታወቀ። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በሊቢያ ዛዋራ ዳርቻ አካባቢ ሰኞ ዕለት የተሳፈሩበት ጀልባ ሞተር በመፈንዳቱ በተከሰተው አደጋ 37 ሰዎች መትረፋቸውንና ቢያንስ የ45 ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል። በሕይወት የተረፉት አብዛኞቹ ሰዎች ከሴኔጋል፣ ማሊ፣ ቻድ እና ጋና የመጡ መሆናቸውንና በአካባቢው ዓሣ አጥማጆች ከአደጋው ተርፈው ወደብ አቅራቢያ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተገልጿል። ይህንን አስከፊ አደጋ ተከትሎ አገራት ለአደጋ ጊዜ የሚሰጡት ምላሽ ላይ አስቸኳይ ክለሳ እንዲደረግ ሁለቱ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል። በሊቢያ የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ተልእኮ ሓላፊ ፍሬዴሪኮ ሶዳ በትዊተር ገጻቸው በለቀቁት ጽሑፍ፣ “በአካባቢው በአውሮፓ ኅብረት የሚመራ ምንም ዓይነት የፍለጋ እና አደጋ ታዳጊ የለም” ብለዋል። አያይዘውም፣ “የፍለጋ እና የመታደግ አቅማችንን ካላጠናከርን በስተቀር የከፉ አደጋዎች መከሰታቸው አይቀሬ ነው” ሲሉ በሜዲትራኒያን ባሕር ዳርቻ የሚገኙ አገራት ሁኔታ በመጥቀስ ተናግረዋል። የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች የውኃ ላይ ጉዞ ባለሥልጣናት ሰዎች ወደ አውሮፓ ለመግባት አደገኛ በሆነው የጀልባ ጉዞ ላይ እያሉ አደጋ ገጥሟቸዋል ሲባሉ የሚሰጡት ምላሽ በቂ አይደለም በማለት በተደጋጋሚ ወቀሳ እንደሚያቀርቡ አልጀዚራ ዘግቧል። በያዝነው እ.አ.አ 2020 ብቻ በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ በተከለሰቱ አደጋዎች ቢያንስ 302 ሰዎች መሞታቸውንና እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ሺህ እንዲያሻቅብ ማድረጉን ዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት ጠቅሷል።