March 20, 2023
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት የአቶ በቀለ ገርባ እና ጃዋር መሐመድን ጨምሮ የ14 ተጠርጣሪዎችን የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ለመስማት ለዛሬ ይዞት የነበረውን ቀጠሮ ለሌላ ጊዜ አሸጋግሯል። ምስክሮችን የመስማት ሂደቱ ለሌላ ጊዜ የተሸጋገረው ግጭት በመቀስቀስ ወንጀል ከተጠረጠሩት የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች መካከል አምስቱ በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ማቆያ በመግባታቸው የተጠርጣሪ ጠበቆች የምስክር ሂደቱ ይቋረጥልን በማለት በማመልከታቸው ነው። ከዚህም ባሻገር አቶ በቀለ ገርባ እና ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንዲደረግላቸውም ጠበቆቹ ጠይቀዋል። ከአያያዝ ጋር በተያያዘ ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማረፊያ ከሚገኙት ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነ ውጪ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የአያያዝ ችግር እንዳለባቸው አመልክተዋል። በተለይ ከቤተሰብ ልብስ እና ምግብ እየቀረቡላቸው እንዳልሆነ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ህግንም ምላሽ ሰምቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት በማቆያ የሚገኙ አምስቱን ጨምሮ የሌሎችም በቀጠሮ ላይ ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተካሂዶ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአስቸኳይ ውጤታቸውን እንዲያሳውቅ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል። ከአያያዝ ጋር በተገናኘም ለተነሳው አቤቱታ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ የተሰጠበት በመሆኑ የፌደራል ፖሊስ የሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤትን ተከትሎ የዐቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ለመጪው ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።