June 4, 2023
በአካባቢያቸው ባጋጠማቸው የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ችግሩን ለማቃለል በ361 ሚሊዮን ብር በጀት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል። በከተማው የቀበሌ 2 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ከድጃ ኢብራሂም፣ የውኃ አቅርቦቱ የተቆራረጠ በመሆኑ አንድ ጀሪካን ውኃ በአምስት ብር ገዝተው ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጸው፣ ችግሩ ለረጅም ጊዜ በመዝለቁ በፍጥነት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል። በከተማው የዓዲ ሓቂ ቀበሌ ነዋሪ መምህር አባዲ ገ/ሕይወት በበኩላቸው ከተማው እየሰፋ፣ በሁለት ሳምንት ውስጥ አንድ ጊዜ ውኃ የሚያገኙ ከመሆኑ በተጨማሪ የአቅርቦት ቆይታው ለውስን ሰዓታት ብቻ በመሆኑ መቸገራቸውን አስታውቀዋል። የመቀሌ ከተማ ውኃ እና ፍሳሸ ጽ/ቤት አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ገ/መስቀል ረዳ የከተማው መስፋት እና ሕዝብ እየጨመረ በመሆኑ እንዲሁም አንዳንድ ያረጁ መስመሮች እየፈነዱ የውኃ እጥረት ችግር ማስከተሉን ገልጸዋል። ተጨማሪ የውኃ ምርት በማቅረብ የአገልግሎት አሰጣጠን ለማሻሻል እና የውኃ ብክነትን ለመከላከል የመስመር ጥገና እና 60 ኪሎ ሜትር አዲስ መስመር ለመዘርጋት ከ361 ሚልዮን ብር በላይ መመደቡን ገልጸዋል። በከተማ አስተዳደሩ የውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ይብራህ ተድላ በበኩላቸው የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያሻሻሉ ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል። የተጀመሩ ሥራዎች የውኃ አቅርቦቱ በማሻሻል በከተማው የተለያዩ አከባቢዎች የሚስተዋለውን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት መቆራረጥ ችግር እንደሚያቃልል ይጠበቃል። በአስተዳደሩ አሁን ያለውን የቀን የውኃ ምርት ከ32 ሺህ ሜትር ኪዩብ ወደ 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ ከፍ ለማድረግ ተጨማሪ ሦስት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ እና አንድ ሺህ ያረጁ የውኃ ቆጣሪዎች እንደሚቀየሩም ገልጸዋል።