July 8, 2020

ነብዩ መሐመድን አጥላልታችኋል በሚል ሞት የተፈረደባቸው ባልና ሚስት ክርስቲያኖች ድረሱልን እያሉ ነው

June 3, 12:26 pm | @BBC Amharic


ሻጉፋ ካውሳር እና ባለቤቷ ሻፍቃት ኢማኑኤል ላለፉት 6 ዓመታት በእስር ላይ ነበሩ። ሞት የተፈረደባቸው ከዓመታት በፊት ሲሆን አሁን የመጨረሻውን የይግባኝ ውሳኔን እየጠበቁ ነው ያሉት። በማዕከላዊ ፓኪስታን ጉጅራ አውራጃ ተወላጅ የሆኑት ባልና ሚስት ክርስቲያኖች እጅግ በድህነት ሕይወታቸው የሚመሩ ናቸው። ዛሬ ረቡዕ የላሆር ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ፍርዳቸው ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ጠበቃቸው ሰይፍ አልማሉክ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሁለቱን ክርስቲያኖች ሞት ያስፈረደባቸው ጉዳይ በቂ ማስረጃ ያልቀረበበትና የተምታታ ነው። ጠበቃ አልማሉክ ከዚህ ቀደም የዓለም መነጋገርያ የነበረችውና የሞት ፍርድ ተወስኖባት በመጨረሻም እንዲቀለበስ የተደረገላት የአሲያ ቢቢ ጠበቃ እንደነበር ይተወሳል። ጠበቃ አልማሉክ እንደሚለው የሞት ፍርዱ ይግባኝ ተቀባይነት የሚያገኝበት እድል ሰፊ ሆኖ ሳለ፤ ነገር ግን ዳኞች በጽንፈኞች አራማጆች ጥቃት ይደርስብናል ብለው ስለሚፈሩ ውሳኔያቸው በተቃራኒው ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ገብቶታል። ባልና ሚስቱን ለሞት ፍርድ የዳረጋቸው በ2014 በስልካቸው ለአንድ በአቅራቢያቸው ለሚገኝ ኢማም ነብዩ መሐመድን የሚያንቋሽሽ ስድብ የጽሑፍ መልዕክት ልካችኋል በሚል ነው። በፓኪስታን የእስልምና ሐይማኖትን ማንቋሸሽና በነብዩ መሐመድ ላይ መሳለቅ የሞት ፍርድ የሚያሰጥ ቢሆንም እስከዛሬ በዚህ ምክንያት ሞት የተፈረደበት ዜጋ የለም። ሆኖም ግን ጽንፈኞች በግል እርምጃ በመውሰድ በዚህ ክስ የሚጠረጠሩ በርካታ ሰዎችን ገድለዋል። የሻጉፋ ወንድም ለቢቢሲ እንደተናገረው ክሱ ውድቅ ሊደረግ ይገባል። ምክንያቱም ባልና ሚስቱ እንኳን ነብዩ መሐመድን ሊሳደቡ ቀርቶ የስልክ የጽሑፍ መልዕክት ለመጻፍ የሚያስችል ችሎታም የላቸውም። ሻጉፍታ በአንድ የክርስቲያን ትምህርት ቤት ህጻናት ተንከባካቢ ስትሆን ባሏ ግን በከፊል ሰውነቱ የማይታዘዝለት ስለሆነ ከቦታ ቦታ እንደልብ መንቀሳቀስም አይችልም። ወንድምየው ሁለቱን ፍርደኞች ለመጎብኘት እስር ቤት በሄደበት ነገሩኝ እንዳለው ባልና ሚስቱ ድርጊቱን እንደፈጸሙ እንዲያምኑ ከፍተኛ ግርፋት ተፈጽሞባቸዋል። ባልና ሚስቱ 4 ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ልጆቻቸው በወላጆቻቸው መታሰር ምክንያት ከፍተኛ የሥነልቦና ጉዳት ላይ ናቸው ተብሏል። ጆሴፍ እንደተናገረው ልጆቻቸው ሁልጊዜም እያለቀሱ ነው የሚኖሩት። ወላጆቻችውን ለማየት ናፍቀዋል። በፓኪስታን ይህ ሐይማኖት የማጥላላት ክስ ዜጎች የሚጠሉትን ሰው ለማጥቃት ጭምር ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። በባልና ሚስቱ ጉዳይም ይኸው ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አለ። የሞት ፍርደኞቹ ጠበቃ እንደሚለው ባልና ሚስቱ ጎረቤታቸው ጋር ቅራኔ ስለነበራቸው ይኸው ክፉ ጎረቤት በሻጉፋ ስም አዲስ ሲም ካርድ በመግዛት ለኢማሙ ያንን ጸያፍ መልዕክት ልኳል። በዚህም ጎረቤቱን ሊበቀል ችሏል። በፓኪስታን የእስልምና ሐይማኖት ላይ መሳለቅና ነብዩ መሐመድን ማንቋሸሽ ለሞት ፍርድ የሚዳርግ ቢሆንም ተግባራዊ ሆኖ ግን አያውቅም። በርካታ ክሶች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ይደረጋሉ። ሆኖም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞዎች ይቀጣጠላሉ። ባለፈው ዓመት አሲያ ቢቢ በተባለች ክርስቲያን ወጣት የተላለፈው የሞት ፍርድ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ በመላው ፓኪስታን ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል። ቢቢ በመጨረሻው በካናዳ ጥገኝነት እንድታገኝ ተደርጓል። እነዚህ ባልና ሚስት የሞት ፍርደኞ በለስ ቀንቷቸው ነጻ ቢደረጉ እንኳ በፓኪስታን መቆየት ለሕይወታቸው አደጋ ስለሚሆን ጥገኝነት ወደሚያገኙበት አገር ይወሰዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በፓኪስታን የክርስቲያኖች ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ 2 እጅ እንኳ አይሞላም። አንዳንዶች የሚደርስባቸውን በመፍራት ሐይማኖታቸውን ወደ እስልምና ለመለወጥ ይገደዳሉ።