July 8, 2020

በኮሮና ቫይረስ መከሰት የተቋረጠውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው

May 26, 10:51 am | @huleAddis


ኤጀንሲው በቴክኖሎጂ የታገዘ የቤት ውስጥ ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጿል። በየትምህርት ክፍሉ የመማሪያ ጽሁፎች መዘጋጀታቸውንና በአገሪቷ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ተደራሽ በማድረግ ለማሰልጠን እየተሰራ መሆኑን የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበራ አባተ ተናግረዋል። ተቋማቱ የሰልጣኞችን ዝርዝር በመያዝ ጽሁፎቹ እንዲደርሷቸው የማድረጉን ስራ እየሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል። ኮቪድ-19 በአገር ውስጥ ከተከሰተ ጀምሮ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ለኀብረተሰቡ መድረሳቸውን ያወሱት አቶ አበራ በአንጻሩ የኢንተርፕራይዞች ገበያ በመቀነሱ የባለሙያ ምክርና የቴክኖሎጂ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል። በዚህም 2 ሺህ ለሚጠጉ ኢንተርፕራይዞች የምክር አገልግሎት፤ 900 ለሚሆኑትም የቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉን ገልጸዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ለሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አስረድተዋል። ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የንፅህና መጠበቂያዎችና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች ለኀብረተሰቡ በነጻ መከፋፈሉንም ጠቅሰዋል። የሆስፒታል አልጋዎች፣ የእጅ መታጠቢያ ሳሙናዎች፣ የእጅ ጓንትና ሌሎች ቁሳቁሶች እየተመረቱ እንደሆነም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ የቴክኒክ ባለሙያዎች የመተንፈሻ መሳሪያ ተሰርቶ ሙከራ እየተካሄደበት እንደሆነም ጠቁመዋል። ኤጀንሲው እስካሁን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ቁሳቁሶችና 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማድረጉን ገልጸዋል። ENA