September 28, 2020

ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚያስችሉ ፈጠራዎችን ያቀረቡ ተወዳዳሪዎች የሽልማት ስነ ስርዓት ተካሄደ

May 22, 10:40 am | @Walta


የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ጋር ባደረጉት የድጋፍ ስምምነት እና በመንግስት እገዛ ሲካሄድ የነበረው የ ‘Covid-19 technology solution challenge’ ውድድር አሸናፊዎች ተለይተው ታውቀዋል። ለውድድሩ ከተመዘገቡት አመልካቾች በሚኒስትሪያል ግብረኃይሉ በሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴ ተወዳድረው በአጭር ጊዜ ተተግባሪና መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉት ምርጥ ፕሮጀክቶች ተለይተው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።። ትላንት ፍጻሜውን ያገኘውን የውድድር ሂደት በንግግር የከፈቱት የኢኖቬሽን ምርምር ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ ውድድር በችግር ወቅት መፍትሔ ማመንጨት የሚችሉ የፈጠራ ባለሞያዎች እንዳሉን ያመላከተ ነው ብለውታል። በውድድሩ ተሳትፈው ለውጤት የበቁትን አመልካቾች እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት አቶ ሲሳይ ተቋሙ አገራዊ ችግርን ፈጠራን በመጠቀም በአገር በቀል አስተሳሰብ ለመፍታት የያዘውን ጥረት የሚያግዝ ስንቅ አስገኝቷል ብለዋል። የእውቅና እና የሽልማት ስነ ስርዓት ተሳታፊዎችን ለመደገፍና ለማበረታታት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጎን የተሰለፉትን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተወዳዳሪዎች ላሳዩት ቀና ተሳትፎ አመስግነው የቀረቡትን የፈጠራ ውጤቶች ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት ለመቀየር እንሰራለንም ብለዋል፡፡ ለአንድ ወር በዘለቀው በዚህ የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር ልየታ ሂደት በጠቅላላው 446 ፕሮጀክቶች ቀርበው ከፍተኛ የቴክኒክ ግምገማውን ያለፉ 30 ፕሮጀክቶች ወደቀጣዩ የግምገማ ሂደት ያለፉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን አዋጭነታቸው የተረጋገጡ 12 ፕሮጀክቶች ተመርጠዋል፡፡ በውድድሩ ፈጠራዎችን ላቀረቡ ባለሙያዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና አላቸው ሲሉ የገለጹት አቶ ግዛቸው ሲሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ ናቸው። አቶ ግዛቸው መሰል ችግር ፈች ፕሮጀክቶችን ለማገዝ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ በመዝጊያ ንግግራቸው፥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል የቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦች በሃገር ደረጃ እምቅ የፈጠራ ሃብት እንዳለ የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም የተመረጡትን ፕሮጀክቶች ወደመሬት በማውረድ ህብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ የተሟላ ድጋፍ እንደሚደረግ እና ሌሎች በግሉ ዘርፍ ያሉ ተቋማትም ፈጠራዎቹ ወደ ንግድና ሐብት ፈጠራ እንዲቀይሩዋቸው ሚኒስትር መስሪያቤቱ ሚናውን እንደሚወጣ አስገንዝበዋል፡፡ (ምንጭ፡-የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)