June 4, 2023

የሕገ መንግሥቱን ክፍተት በሕገ መንግሥት ትርጉም የመመለስ ጅማሮ የገጠመው ተቃርኖ

May 11, 9:57 am | @huleAddis


‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፤›› የሚል ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) ላይ ሠፍሮ ይገኛል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት ሥልጣን ላይ የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በእነሱ የተቋቋሙ ሥራ አስፈጻሚ የፈዴራልና የክልል መንግሥታት የሥልጣን ዘመን በመጪው መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጠናቀቃል። የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያገባድዱት የሥልጣን አካላት በሕዝብ ምርጫ መተካት ያለባቸው ቢሆንም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እየተሠራጨ በመሆኑ፣ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የነበረው አጠቃላይ ምርጫ እንዲሰረዝና አገሪቱም የሕዝብ ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንድትተዳደር አስገድዷታል። ከላይ የተገለጸው ነባራዊ ሁኔታ ቢኖርም የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3)፣ ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማንኛውም አኳኋን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፤›› በማለት የክልከላ ድንጋጌውን አሥፍሯል። ይሁን እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ ማድረግ ባይቻል ምርጫ እንዴት እንደሚራዘም፣ ወይም አገር እንዴትና በማን እንደምትተዳደር ሕገ መንግሥቱ ከዝምታ ወጪ ያስቀመጠው ግልጽ ድንጋጌ አይገኝም። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማካሄድ ሲያደርገው የነበረውን ዝግጅት በማቋረጥና አውጥቶት የነበረውን አጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቋል። ምክር ቤቱም ከሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ በኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና ተያያዥ ዕክሎች ምክንያት ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይችል በቀረበለት ሪፖርት ላይ የተወያየ ሲሆን፣ በወቅቱም የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ቫይረሱ በኢትዮጵያ ያለው የሥርጭት ሁኔታ ከክልል ክልል የተለያየና በወረርሽኝ ደረጃ በኢትዮጵያ አለመከሰቱን በመግለጽ የቦርዱን ውሳኔ ተቃውመዋል። የቫይረሱ ሥርጭት የምርጫ ዝግጅቶችን ለአብነትም የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማሠልጠን፣ የምርጫ ቁሶችን በማሳተም፣ በማጓጓዝና በሌሎች ዝግጅቶች ላይ የፈጠረውን ዕክል በወቅቱ ያስረዱት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ከማስፈጸም ውጪ የቫይረሱን የሥርጭት ደረጃ የመገምገም ኃላፊነትም ሆነ ብቃት እንደሌለው አስረድተዋል። ነገር ግን ቫይረሱ በኢትዮጵያ ያለውን የሥርጭት ሁኔታና የሥጋት ደረጃ በተመለከተ ከጤና ሚነስቴርና ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት መረዳታቸውን፣ መንግሥትም በአገር አቀፍ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣቱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ምርጫውን ለማካሄድ ቦርዱ እንዳልቻለ አስረድተው ነበር። ምክር ቤቱ ቦርዱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተወያይቶ የቦርዱን ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ከተቀበለ በኋላ፣ ምርጫውን ለማካሄድ ባለመቻሉ የሚፈጠረው የሥልጣን ክፍተት ሕገ መንግሥታዊና የአገረ መንግሥቱን ሉዓላዊነት በሚያስጠብቅ መንገድ የሚሸፈንበትን የመፍትሔ አማራጭ አጥንቶ እንዲያቀርብ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። ቋሚ ኮሚቴውም ለተወሰኑ ቀናት ሕጋዊ የመፍትሔ አማራጮችን የመለየት ሥራ አከናውኖ፣ የውሳኔ ሐሳቡን ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ አቅርቧል። ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ለቀጠረው የሕግ ክፍተት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም መፍትሔ እንዲሰጥበት የሚጠይቅ ነው። ‹‹የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ በማለት ሲደነግግ፣ በአንቀጽ 58(3) ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል ሲል ታሳቢ ያደረገው፣ መደበኛና ጤናማ የሆነውን ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ነው፤›› በማለት ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳቡ አመልክቷል። በሌላ በኩል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚታወጅ፣ ይህም የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የሚያስገድድ ጦርነት ቢከሰት፣ የተፈጥሮ አደጋና የሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል። ነገር ግን ምርጫ በሚደረግበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰትና በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን፣ የምርጫ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ምክር ቤቶችና ሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የሥልጣን ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱ ምላሽ ባለመመለሱ የገጠመውን ችግር በመፍታት ረገድ ሕገ መንግሥቱ ችግር ክፍተት አለበት የሚያስብል ነው። ‹‹በመሆኑም ከፍ ብለው የተገለጹትን ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱ ዓለማና ግቦች፣ እንዲሁም መሠረታዊ መርሆዎች ጋር በማገናዘብ ትርጉም እንዲሰጣቸው በአብላጫ ድምፅ ወስነናል፤›› በማለት ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል። በዚህ መሠረት በተካሄደ ውይይት የትግራይ ክልል ተወካዮች የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ኢሕገ መንግሥታዊ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል። ከእነዚህም መካከል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንትና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አዲስ ዓለም ባሌማ (አምባሳደር) ይጠቀሳሉ። እሳቸው ባነሱት የመከራከሪያ ነጥብ በሕገ መንግሥቱ ላይ የትርጉም ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለው ለትርጉም አሻሚ የሆነ ድንጋጌ ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል። የተነሳውን ጉዳይ በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ የትርጉም ጥያቄ ማንሳት ሕገ መንግሥታዊ አለመሆኑን በማውሳት ተከራክረዋል። ምክር ቤቱ በዚህ መንገድ የራሱን ሥልጣን ለማራዘም መሞከሩ የሕገ መንግሥት ጥሰት እንደሆነም ተናግረዋል። የመናገር ዕድል የተሰጣቸው ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት አዲስ ዓለም (አምባሳደር) የሚወክሉት ፓርቲ ሕወሓት በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ኖሮት በቆየባቸው ዓመታት፣ ፈጽሟቸዋል የሚሏቸውን የሕገ መንግሥት ጥሰቶች በማንሳት ትችቶችን ሰንዝረዋል። አንድ የምክር ቤት አባል ግን በምክር ቤቱ አባላት መካከል የቃላት ድንጋይ መወራወሩ እንዲቆም በማሳሰብ፣ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብም ሆነ ምክር ቤቱ እየተወያየ የሚገኘው ‹‹የሥልጣን ዘመኔ አልቋል፣ ሥልጣን ለማን ላስረክብ በማለት በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መፍትሔ እየፈለገ እንጂ ሥልጣኑን እያራዘመ አይደለም፤›› ሲሉ ተከራክዋል። የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሠረታዊ ይዘት ላይ ካደረጉት ክርክር ይልቅ ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠር የተወራወሯቸው ቃላት ቢበዙም፣ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የነበረው ክርክር በድምፅ ተለይቶ የውሳኔ ሐሳቡ በ23 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም እንዲሰጥበት እንዲመራ ሆኖ ፀድቋል። ከምክር ቤቱ ውጪ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ካካሄደው ክርክር በመለስ፣ ባሉት መድረኮችም በተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ውዝግብ ላይ የፖለቲካ ክርክሩ ተጧጡፎ የቀጠለ ሲሆን፣ በአገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በጉዳዩ ላይ በንቃት እየተሳተፋ ናቸው። የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ሕወሓት ጉዳዩን አስመልክቶ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተወያይቶ ባለፈው ሳምንት ያወጣው መግለጫ፣ እዚህ ላይ ተጠቃሽ ነው። የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ ያለ በቂ ዝግጅትም ሆነ ያለ ግልጽ አጀንዳ የተጠራውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕግ ውጪ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበትን መድረክ ተከትሎ፣ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግናን ሕገወጥ የሥልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ የሚያሳይ ተግባር ነው ሲል ኮንኖታል። ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልጽ መሥፈርት መሠረት አሻሚ ሆኖ ለተገኙ አንቀጾች እንጂ፣ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ ለማራዘም ሊሆን አይችልም፤›› የሚለው ሕወሓት፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፊያ በአስቸኳይ ቆሞ የኮሮናን ወረርሽኝ በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ አገራዊ ምርጫን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ፣ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ አገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ ይመቻች፤›› በማለት ጠይቋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ በተከለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደ ዋዛ እንዲጣልበት፣ እንደማይፈቅድ ሕወሓት በመግለጫው አስታውቋል። የትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ እንደሚሠራና ምርጫን ጨምሮ ይኼንኑ የሕዝቦች መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን፣ በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል። በተጨማሪም መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ሕወሓት በይፋ አስታውቋል። ሌሎች ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት ሆነው ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ፣ ሥልጣን ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት ለተፈጠረው የሕገ መንግሥት ክፍተት በአማራጭነት ያነሱትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ኢሕገ መንግሥታዊ ሲሉ ያወገዙ ሲሆን፣ ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ አማራጮች ሊኖሩ አለመኖራቸውን በመጥቀስ መፍትሔ ያሉትን የፖለቲካ አማራጭ ጠቁመዋል። ትብብር ለኅብረ ብሔር ዴሞክራሲያዊ ፊዴራሊዝም በሚል ስብስባቸውን የጠሩት እነዚህ ሰባት ፓርቲዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲና ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ናቸው። በአማራጭ መፍትሔነት ያቀረቡትም ‹‹የኮሮና ቫይረስ አደጋን በጋራ እየተከላከልንና በሌላ በኩል ለምርጫ እየተዘጋጀን ወረረሽኙ አልፎ (ተወግዶ) ምርጫ እስክናካሂድ ድረስ የሚፈጠረውን የመንግሥት ሥልጣን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ፣ አገራዊ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነው ብለን እናምናለን፤›› የሚል ነው። አንደኛው የፖለቲካ አማራጭ የሽግግር ወቅት የፖለቲካ አደረጃጀት ቢሆንም፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን ማከናወን ቀላል እንደማይሆን የሚጠቅሱት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አሁን ያለውን መንግሥታዊ መዋቅር ችግሮቹ ተቀርፈው ምርጫ እስኪከናወን ድረስ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ብቻ ማከናወን አለበት የሚል የመፍትሔ አማራጭ አቅርበዋል። በዚህ አማራጭ ላይ ዝርዝር ሁኔታዎችን ለማቅረብ እንደሚችሉ ነገር ግን ከዚህ ውጪ የሚወሰድ ማንኛውም ዕርምጃ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊናና ሕዝባዊ ተቀባይነት ስለሌለው አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስና ብጥብጥ እንደሚወስድ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አቶ ልደቱ አያሌው አሁን የገጠመው ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝን ለመፍታት የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ አማራጭ አለመኖሩን ሲጠቅሱ የሰነበቱ ሲሆን፣ ለዚህም በምክንያትነት የሚያነሱት ‹‹በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማንኛውም አኳኋን የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፤›› የሚለውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3) ድንጋጌ ነው። መፍትሔውም ፖለቲካዊ እንደሆነና ይኸውም ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን ያሳተፈ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህንንም አማራጭ እሳቸው አባል የሆኑበት ፓርቲ ኢዴፓ የሚሳተፍበት አብሮነት የተሰኘ የፖርቲዎች ጥምረት የሚያቀርበው የመፍትሔ አማራጭ ነው። አቶ ልደቱ የሽግግር መንግሥት አማራጭን ከጠቆሙ በኋላ ከፍተኛ ትችት በማኅበራዊ ሚዲያ ያስከተለባቸው ሲሆን፣ ይኼንንም ተከትሎ በሰጡት ማብራርያ የሽግግር መንግሥትን በአማራጭነት ያነሱት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገርን ከቀውስ የመታደግ ቁመና ላይ አይደለም ብለው በማመናቸውና አገርን ለማዳን ተመራጩ መፍትሔ እንደሆነ በማመን መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች አማራጮች የሚቀርቡ ከሆነም ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ ስምምነት ከተደረሰበት መቀበል እንደሚቻል ይገልጻሉ። ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የሚመሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የበኩሉን የመፍትሔ አማራጭ የጠቆመ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 58 (3)ን በማሻሻል አሁን ያለውን መንግሥት ዕድሜ በአንድ ዓመት ማራዘምና ተዓማኒ ምርጫ ማድረግን በመፍትሔነት አቅርቧል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የሽግግር መንግሥት ‹‹የሕዝብን ዘላቂ ጥያቄዎች የማይመልስ በመሆኑ እንደማይቀበለው ገልጾ፣ በአማራጭነት በቀረበው መፍትሔ መንግሥት መር ሽግግር እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። ይህ አማራጭ መዋቅራዊና ሁሉን አካታች ሽግግር ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳው አብን፣ ይህንን ለማሟላትም ሁሉንም ባለድርሻዎች ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ‹ብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን› ሊቋቋም ይገባል ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 29 2012 ዓ.ም. ቀን በሰጡት መግለጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚነሱ የመፍትሔ አማራጮች ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሻቸውም በአንድ በኩል የሕገ መንግሥት ትርጉም አማራጭ ጠቃሚነትንና በሌሎች ፓርቲዎች ለቀረቡ አማራጮች ዝርዝር ማብራርያና ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሽግግር መንግሥት ጥያቄ የሚያነሱ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ ጠንከር ያለ ተግሳፅና ማስጠንቀቂያን የያዘ ነው። የሕገ መንግሥት ትርጉም አማራጭ ሕገ መንግሥታዊና ሕጋዊ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግሩን ለማለፍ የሚተረጎም የሕገ መንግሥት አንቀጽ አለመኖሩን በማንሳት የሚከራከሩ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን ‹‹አውቆ እንዳለወቀ ለመሆን ከወሰነ ሰው፣ ወይም ጥልቅ በሆነ የአላዋቂነት አረንቋ ውስጥ ከተዘፈቀ ሰው የሚጠበቅ መከራከሪያ ነው፤›› ሲሉ ተችተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት በዚህ መግለጫ መንግሥታቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻውን ብዙ ርቀት መሄድ እየቻለ ወይም በቀላሉ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ እየቻለ፣ ጉዳዩን ለምክክርና ለውይይት ማቅረቡ አሳታፊ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል። ‹‹ሕዝባችን ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት ጊዜ ሥልጣንን ያለ ምርጫና ከሕግ አግባብ ውጪ በሁከትና በብጥብጥ ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ኃይል፣ እንደማንታገስ ከወዲሁ በግልጽ ለመንገር እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት አለን›› ሲሉ ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ሥልጣን የሚከፋፈልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ የለም። የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆንኩ ሥልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፤›› ሲሉ የሽግግር መንግሥት ሐሳብ የሚያነሱትን ተችተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያነሷቸው የመፍትሔ አማራጮች ፈርጀ ብዙና አንዳንዶቹም የማይታረቁ የሚመስሉ ቢሆንም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕገ መንግሥት ምሁራን ግን የሕገ መንግሥት ትርጉም አማራጭ ችግሩን ለመፍታት የተሻላ እንደሆነና በዚህ ውስጥ የሚነሱትን የአሳታፊነት ጉድለቶች ለመቅረፍ ትርጉም የመስጠት ሒደቱ ከሥነ ሥርዓት ሁኔታዎችን ወጣ ብሎ የፖለቲካ ኃይሎችን በውይይቶች በማሳተፍ ሊፈጸም እንደሚገባ ይመክራሉ። በሌላ በኩል አገር የኮሮና ወረርሽኝ አደጋ ተደቅኖባት የዜጎችን ሕይወት መታደግ ሲገባ፣ ባልተገባ መንገድ ሥልጣን ለማግኘት ሲባል ግጭት ለመቀስቀስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን የሚያወግዙ ድምፆች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ተሰምተዋል፡፡ reporter (ዮሐንስ አንበርብር)