June 4, 2023
April 16, 9:37 am | @huleAddis
ቫይረሱ ከተከሰተበትና ለዓለም ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ የዓለምን ማኅበረሰብ ቀልብ የሳበ ሲሆን፣ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሩቅ በሆነችው ቻይና የተከሰተው በሽታ የእያንዳንዱን የዓለም አገር ጓዳ ለማንኳኳት አራት ወራት ብቻ ነው የፈጀው፡፡ ይኼም ዓለም ምን ያህል ከሚባልላት በላይ ቅርብና አንድ መድረክ እንደሆነች ማሳያ ነው በማለት የሚስማሙ በዝተዋል፡፡ በቫይረሱ ምክንያት እየሞቱ ያሉ ሰዎችን ቁጥር ከፍ አድርገው ግምታቸውን በመሥራት ከ100,000 እስከ 200,000 ሰዎች ሊሞቱባቸው እንደሚችሉ በመገመት፣ የተቀረውን ሕዝብ ለማዳን እየዳከሩ የሚገኙት እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ‹‹ቫይረሱ ከምንም በላይ እኩል አድራጊ›› እንደሆነ መረዳታቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ በአውሮፓ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የአገር መሪዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ያደረገው ኮቪድ 19 ጣሊያንን፣ ስፔን፣ ፈረንሣይንና እንግሊዝን እየናጠባቸው ነው፡፡ በአፍሪካም እግሩን ያስገባው ኮቪድ 19 ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ባሉ አገሮች ተንሰራፍቶ ከ15,000 በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ይኼ ከፍተኛና ውስብስብ የሆነ የጤና ሥርዓትና ዝግጁነት አላቸው የሚባሉ ያደጉ አገሮችን እየፈተነ የሚገኘው ቫይረስ፣ የኃያላን አገሮች እርስ በርስ ትችንና ወቀሳን ያስቀረ ሳይሆን ያባሰ ሆኗል፡፡ በዚህ የቃላት መወራወርና ወቀሳ መሀል የሚገኙት የዓለም ጤና ድርጅትና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ከወላፈኑ ተቃምሰዋል፡፡ ይኼ የኃያላን አገሮች የቃላት ውርወራና ወቀሳ በዋናነት በአሜሪካና በቻይና መካከል የሚስተዋል ሲሆን፣ በተለይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቻይና የቫይረሱን ሥርጭትና አስከፊነት በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ ስላልሰጠች ጥፋቱ የከፋ ሆኗል ሲሉ ጠንካራ ነቀፌታ ይሰነዝራሉ፡፡ ለዚህም የዓለም ጤና ድርጅትና ዳይሬክተሩ ቴድሮስ (ዶ/ር) ተባባሪ ናቸው በማለት የ‹‹ወንጀሉ›› ተካፋይ ያደርጓቸዋል፡፡ በሌላ ወገን የምትገኘው ቻይና በበኩሏ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ አማካይነት ባወጣችው መግለጫ፣ ምናልባትም ቫይረሱ በአሜሪካ መከላከያ ሠራዊት አማካይነት ወደ ቻይና የመጣ ሊሆን ይችላል በማለት መላምታዊ ወቀሳ ሰንዝራለች፡፡ ይኼም ራሱን የቻለ ቁጣንና ወቀሳ አስከትሏል፡፡ ይሁንና በተለይ በአሜሪካና በቻይና መካከል እየታየ ያለው መወቃቀስ በዋናነነት በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያተኮረና ዋና ዳይሬክተሩም ሥራቸውን እንዲለቁ እስከ መጠየቅ የደረሰ እንደ መሆኑ መጠን፣ ዋና ዳይሬክተሩ ምላሽ እንዲሰጡበትና ወቀሳውን እንዲያጣጥሉ፣ እንዲሁም ሌሎች ማስፈራሪያዎች እየደረሷቸው እንደሆነ እንዲናገሩ አድርጓል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት ሥራውን በጠቅላላ ነው ያበላሸው በማለትና ቻይናን ማዕከል ያደረገ ነው በሚል ወቀሳ፣ አገራቸው ለዓለም ጤና ድርጅት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ለመቀነስ እንደሚያስቡ ገልጸዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትም በእጅጉ ለቻይና ያደላ ነው ሲሉም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡ ወቀሳውንና ትችቱን እንዲሁም ከሥራቸው እንዲለቁ እየቀረበላቸው ያለውን ጥሪ በተመለከተ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ምላሽ የሰጡት ቴድሮስ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኔ በግሌ ምንም አይመስለኝም፡፡ ሕይወት ማዳኑ ላይ ማተኮርን እመርጣለሁ፤›› ብለው፣ ‹‹ሰዎች እየሞቱ እኔ በግል ተጠቃሁ ብዬ ስለምን እጨነቃለሁ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ፡፡ ቴድሮስ በዚህች ዓለም እኮ አንድ ነጥብ ነው፤›› በማለት ያከሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ሙታኖቻችሁን የምትገንዙበትን መግነዝ ካልፈለጋችሁ በስተቀር፣ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ማድረግ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ በማከልም ቻይናና አሜሪካ ይኼንን አደገኛ ጠላት ከማሸነፍ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ በማቅረብ፣ ያለበለዚያ በእሳት የመጫወት ያህል ነው በማለት አሳስበዋል፡፡ በተለይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች የአሜሪካን በር ዝግ ሲያደርጉ፣ ቴድሮስ (ዶ/ር) እንዲህ ያለ ዕርምጃ ማግለልን ይፈጥራልና በጎ አስተዋጽኦ አይኖረውም በማት መከላከላቸውን በመጠቆም፣ የዓለም ጤና ድርጅት የተሳሳተ ውሳኔ በመስጠቱ ዓላማውንም ስቷል በማለት ወቅሰዋል፡፡ ስለዚህም የቫይረሱን ሥርጭት የዓለም ሥጋት ነው በማለት ወረርሽኝ መሆኑን ሳያውጁ መቅረታቸውን ስህተት ነበር በማለት፣ ‹‹ከወራት አስቀድሞ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር፡፡ ቀድመው ሊያውቁ ይችሉ ይሆናል፣ ማወቅ ነበረባቸው፣ ምናልባትም ቀድመው አውቀው ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ምንም እንኳን በኋላ ንግግራቸውን ቢያርሙትም፣ 15 በመቶ የዓለም የጤና ድርጅት በጀት የምትደጉመውን አሜሪካ ድጋፍ በድጋሚ እንደሚያጤኑት ተናግረዋል፡፡ ብራድሉ ታየር የተባሉ በቴክሳስ አንቶኒዮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰርና ‹ሲቲዝን ፓወር ኢንሼቲቭ ፎር ቻይና› የተባለ ተቋም ምክትል ፕሬዚዳንት ሊያንቻዎ ሃን በጋራ ዘ ሂል በተሰኘው የአሜሪካ የዜና አውታር ባወጡት ጽሑፍ፣ ቴድሮስ (ዶ/ር) ወረርሽኙን በቸልተኝነት በመምራታቸው ጉዳዩን ካተቀረው ዓለም ከደበቁት ሺ ዢንፒንግ እኩል ተጠያቂ መሆን ይገባቸዋል ሲሉ ደምድመዋል፡፡ ‹‹የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን ለመምራት ብቁ እንዳልሆኑ አሳይቷል፡፡ በእሳቸውም አመራር ሳቢያ ዓለም ቫይረሱን ለማቆም ወይም ጉዳቱን ለመቀነስ የሚያስችል ዕድል አምልጧታል፤›› በማለት የተከራከሩት ሁለቱ ጸሐፍት፣ ‹‹ዓለምን ከወረርሽኝ መከላከል ላይ ማተኮር ሲኖርባቸው ጉዳዩን ፖለቲካዊ በማድረግ፣ የቻይናው ሺ ዢንፒንግ ጥረቶቻቸውን በመደበቅ ኃላፊነትን እንዲሸሹ አድርገዋል፤›› በማለት ወቅሰዋል፡፡ ወደ ቻይና የቫይረሱን ሁኔታና ባህርይ ለመገምገም የሄደው የዓለም ጤና ድርጅት፣ የቻይናን ምላሽ አድንቆና በመረጃ አቅርቦት ረገድ ጥሩ ሥራ እንዳየ በመግለጽ ውዳሴ ማቅረቡን እያነሱ የሚተቹ አልጠፉም፡፡ ይሁንና አገሮቹ መረጃ ካልሰጡ የድርጅቱ አወቃቀር በራሱ አስገዳጅ መረጃ የማግኛ መንገድ ስለሌለው ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል በመግለጽ፣ ጥፋቱን ወደ ዓለም ጤና ድርጅት ማላከክ አግባብ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩ አልጠፉም፡፡ ከ23,000 በላይ ዜጎቿን በቫይረሱ ሳቢያ ያጣችው አሜሪካ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል እ.ኤ.አ. ከ2017 አንስቶ የመከላከያ ሚኒስቴር ማሳሰቡን፣ ቫይረሱ ወደ አሜሪካ ከመግባቱ ሦስት ሳምንታት ቀደም ብሎ ዕርምጃዎች እንዲጠናከሩ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ጆሮ ዳባ ልበስ መባሉ፣ እንዲሁም ከፕሬዚዳንቱ ሳይቀር የሚሠራጩ የነበሩት የተሳሳቱ መረጃዎች ያስከተሉት ጥፋት ስለሚበዛ የዓለም ጤና ድርጅትንና ቴድሮስን (ዶ/ር) የመስዋዕት በግ ለማድረግ የሚያሳዩት መጣጣር ነው ሲሉም የሚወቅሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሚሰነዘሩት ዘረኛ ቃላት የነጩ ዓለም በጥቁሮችና በለዘብተኛ ነጮች ላይ ዕምነት እንዳይጥል፣ በፖለቲካውም ዘላቂ ደጋፊ የሚያስገኝላቸውን መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ዘመቻ ነው በማለት የወቀሱም አልጠፉም፡፡ ‹‹ጥቁርም አሉኝ ኔግሮ እኔ በጥቁርነቴ የማላፍር ነኝ፤›› በማለት ዘረኛ ቃላት መሰንዘራቸውን አጥብቀው የተቃውሙት ቴድሮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹በግል ለሚሰነዘርብኝ ጥቃት ግድ የለኝም፡፡ ግን ከዚህ አልፎ በማኅበረሰብ ደረጃ ሲመጣ ያኔ መስመሩን ያልፋል፣ ሲበቃ ይበቃል፤›› ሲሉ በቁጣ መልሰዋል፡፡ ከዚህ በላይም የግድያ ዛቻዎች ሁሉ እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅትና በዳይሬክተሩ ቴድሮስ (ዶ/ር) ላይ የሚሰነዘሩ ውንጀላዎች ምቾት የነሳቸው የተለያዩ አገሮች መሪዎች ለተቋሙና ለዳይሬክተሩ አጋርነታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የድጋፍ ፊርማ ሲያሰባስቡ የተስተዋሉም በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይ የዳይሬክተሩን ብቃትና ለቻይና ወግነዋል መባሉን ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ የአለርጂና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶኒ ፎቺ፣ ‹‹ቴድሮስ እጅግ ብቁ የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ አውቃቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ የዓለም ጤና ድርጀት ከችግሮች የፀዳ ተቋም ነው የሚል ካለ ድርጅቱን አያውቀውም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በእርሳቸው አመራር ወቅት እጅግ የሚደነቅ ሥራ ሠርተዋል፤›› ሲሉ ደግፈዋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው፣ ‹‹የዓለም ጤና ድርጅት በቴድሮስ (ዶ/ር) አመራር ወቅት የሚጠበቅበት ነገር ሁሉ በምንፈልገው ወቅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ፋታ ልንሰጠው ይገባል፤›› በማለት ድጋፋቸውን ያሳዩ ሲሆን፣ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከድርጅቱና ከቴድሮስ (ዶ/ር) ጎን መቆማቸውን ከየትኛውም የኢትዮጵያ መሪም ሆነ ባለሥልጣን ወይም ተቋም ቀደም ብለው በድጋፍ መልክ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በዚህም የናይጄሪያ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ አፍሪካና የናሚቢያ ፕሬዚዳንቶች ቀዳሚ ነበሩ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ አመራር ላይ እያደረገ ያለው ዘመቻ እንዳስደነቃቸው የገለጹት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሐመት ሲሆኑ፣ የአፍሪካ ኅብረት ለተቋሙና ለዳይሬክተሩ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም በተመሳሳይ ባወጣው መግለጫ ለድርጅቱና ለዳይሬክተሩ ድጋፉን ቸሯል፡፡ ሪፖርተር