March 31, 2020

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፏን እንደምታጠናክር አስታወቀች

March 25, 12:02 pm | @Walta


አጋጣሚው ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር፣ ወንድማማችነትና ወዳጅነት በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነም ተገልጿል። የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ አንስቶ ቻይና ባላት አቅም በተለያዩ መንገዶች ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች እንደሆነም የኤምባሲው መግለጫ አመልክቷል። ኤምባሲው በአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የሚገኙ የቻይና ባለሙያዎች በማዕከሉ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ሰዎች ግንዛቤያቸው እንዲያድግና ቫይረሱን የመከላከል አቅም የሚገነቡ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ያደረገ መሆኑን ገልጿል። በኢትዮጵያ የሚገኘው የቻይና አፍሪካ የቢዝነስ ምክር ቤት ቢሮ ለጤና ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት 22 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የምርመራ መሳሪያና የሙቀት መለኪያ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል። በኢትዮጵያ የሚገኘው የቻይና ወታደር የጤና ባለሙያዎች ቡድን ለኢትዮጵያ አቻዎቻቸው የኮሮናቫይረስ ምልክቶች፣ ስጋቶችና ባህሪውን አስመልክቶ ገለጻና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውም ተመልክቷል። ይሄም ኢትዮጵያና ቻይና ቫይረሱን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እያደረጉት ያለውን ትብብር የሚያሳይ ነው ተብሏል። የ”ቢጂአይ እና ማሞዝ ፋውንዴሽን” በጋራ በመሆን 30 ሺህ ዶላር ወጪ የተደረገበት የመመርመሪያ መሳሪያ ለጤና ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ድጋፍ አድርገዋል። የአሊባባ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ማ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ለመከላከል ለአፍሪካ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን የምርመራ መሳሪያ፣ 6 ሚሊዮን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እና 60 ሺህ መከላከያ ልብሶች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር። በዚሁ መሰረት ከመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የድጋፍ ቁሳቆሶቹ ወደ አዲስ አበባ መግባት የጀመሩ ሲሆን ድጋፉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ለአፍሪካ አገራት በመሰራጭት ላይ ይገኛል። የቻይና የጤና ባለሙያዎች ከአፍሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ባለሙያዎችና ከአፍሪካ አገራት ጋር በቪዲዮ ኮንፍረንስ ውይይት በማካሄድ የመረጃና የልምድ ልውውጥ መስጠታቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። የቻይናው ሀዋጂያን ዓለም አቀፍ ድርጅት (የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ) 102 ሺህ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ፣ 40 የሙቀት መለኪያ በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት ድጋፍ ማድረጉም የሚታወስ ነው። በተጨማሪም ድርጅቱ 2 ሚሊዮን ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የጤና ግብአቶችና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉም አይዘነጋም። የኮሮናቫይረስ ድንበር የለሽ በመሆኑ ኢትዮጵያም ቫይረሱን ለመከላከል እየወሰደቻቸው ያሉት እርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው ብሏል ኤምባሲው በመግለጫው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ቻይናውያን ኢትዮጵያ ያስተላለፈቻቸውን መመሪያዎች በመከተል ተምሳሌት እንደሚሆኑም ተገልጿል። የቻይና ህዝብና መንግስት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኤምባሲው በመግለጫው አረጋግጧል።