March 31, 2020

የጉምሩክ ኮሚሽን በስምንት ወራት 74.1 ቢሊዮን ብር ሰበሰበ

March 24, 12:04 pm | @Walta


የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር ትውውቅና ውይይት ሲያካሂዱ እንደተገለጸው ኮሚሽኑ በገቢ አሰባሰቡ በስምንት ወራት ውስጥ 73.9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 74.1 ቢሊዮን ወይም 100.1 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡ የተቋሙን አደረጃጀት፣ የስራ ክፍሎችንና የተቋቋሙበትን አላማ፣ የተቋቋሙት የስራ ክፍሎች በስምንት ወር ውስጥ ያከናወኗቸውን ዋና ዋና ተግባራትና በስምት ወራት ውስጥ ማከናወን ሲገባቸው ያላከናወኗቸውን ስራዎችን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ ሪፎርም/ የለውጥ ስራዎችን መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ ስላካሄዳቸው የለውጥ /የሪፎርም ስራዎች፣ የተያዙ የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድ ቅደም ተከተል በአይነትናየገቢና ወጭ ኮንትሮባንድ በቅርንጫፍ ጽ/ቤት ቅድም ተከትል ምን እንደሚመስል ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቀበታ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ከቅንጅት ስራ ጋር ተያይዞም የኮንትሮባንድ ግብረሃይልና ሀገራዊ የታክስ ግብረሀይል፣የኤሌክትሮኒክስ አንድ መስኮት አገልግሎት ግብረሀይል፣ የሎጅስቲክስ ሴክተር መሻሻያ ስትሪንግ ኮሚቴ፣ አለማቀፋዊ ድርጅቶች ከአህጉራዊና ከአገራት ጋር ያሉ ቅንጅታዊ አሰራርና እያከናዎኗቸው ያሉትን ተግባርና ያሉባቸውን ክፍተቶች በተመለከተም አቶ ደበሌ ቀበታ ገለጻ አድርገዋል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን የአስር አመት ስትራቴጅክ እቅድ፣ ጉምሩክን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጅዎችና ፕሮጀክቶች መቅረጽ፣ የሰው ሀይልሳ ሙሌትና አቅም ማሳደግ፣ የተጀመረውን የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አጠናክሮ ማስቀጠልና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ያነሱት ኮሚሽነሩ እኒህ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ ጠይቀው በሙሉ አመራሩና ሰራተኛው ስም የእንኳን ደህና መጡ መልዕክት ለሚኒስትሩ አስተላልፈዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌውም ተቋሙ ቀደም ሲል ይታወቅበት የነበረውን ጥሩ ያልሆነ ስም መላው አመራርና ሰራተኛ ተባብሮ መቀየር እንደቻለው ሁሉ የያዘውን ከፍታ ይዞ እንዲቀጥል የሚኒስተር መስሪያቤቱ አመራሮችና መላው ሰራተኛ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር ለውጤት ለመስራት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የሚቆጠርና የሚታይ ስራ የሚሰራበት መስሪያ ቤት እነንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱን ቀንና ሰዓት በትብብር፣ በቅንነትና በትጋት በመስራት የምንፈልገውን ውጤት ስራንና የደንበኞቻችንን እርካታ መለኪያ አድርገን ማምጣት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ መረጃው የገቢዎች ሚኒስቴር ነው፡፡