March 31, 2020

የኮሮና ፈተና፣ አልተጀመረም ገና

March 22, 8:03 pm | @DW


ኮሮና ቫይረስ የዓለምን ሥልጣኔ በእንብርክኩ እያስኬደው ነው። ጥር አጋማሽ ላይ አንድ አገር ውስጥ፣ 100 ሰዎች ብቻ ነበሩ በኮሮና ቫይረስ የተያዙት። በሁለት ወር ውስጥ ከ250 ሺሕ ሰዎች በላይ በቫይረሱ ተይዘው፣ ግማሹ አገግመዋል። ከዐሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ሞተዋል። የቫይረሱ ስርጭት 185 አገሮችን አዳርሷል። በቻይና ዉሃን ከተማ የተከሰተውና ኮቪድ19 በሚል ሥም የሚታወቀው የኮሮና ቫይረስ በሽታ አውሮፓ እና አሜሪካን አዳርሶ በአፍሪካም እየተንሰራፋ ነው። የተሻለ የሕክምና እና የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን ምዕራባውያንን ያንበረከከው ኮሮና፣ አፍሪካን እንዲሁም ኢትዮጵያን እንዴት ያደርጋት ይሆን? ከነጣልያን ስህተት ይማራሉ ወይስ ካለፈ በኋላ ይፀፀታሉ? በድህነት ላይ በሽታ ኮቪድ19 የጤና ስርዓታቸው የዳበሩ አገራትን ሳይቀር አንበርክኳል። መንግሥታት ዜጎች በየቤታቸው እንዲቆዩ ሲወስኑ የንፅሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለመግዛት እርስበርስ እስከ መደባደብ ደርሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ሰው በቫይረሱ መያዙ ከተነገረ በኋላ የተስተዋለው ነገር ጥቂት የከተማ ነዋሪዎች በየሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ያሉ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አጥረግርገው ሲወስዱ፥ ብዙኀኑ ግን እንደተለመደው በአውቶቡስ እና ሚኒባስ ታክሲ ተጋፍቶ መሔዱን መቀጠሉ ነው። ለድሃ አገራት ትልቁ ፈተና ይኼው ነው። ይህንን ቀድሞ መተንበይ ቀላል ነገር ቢሆንም፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቀውሱ የተዘጋጀ አይመስልም። እንዲያው በደፈና ለሕዝብ ግንኙነቱ እየተጋ ነው። የመንግሥትን ቸልተኝነት በድፍረት ለመናገር በቂ ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው እና ትልቁ ቸልተኝነት ቦሌ አየር መንገድ ከውጭ የሚገቡ መንገደኞች ይደረግላቸው የነበረው ምርመራ (ያውም ከተደረገ) የይሥሙላ መሆኑ ነው። ሌላው፣ አዲሱ ገዢ ፓርቲ የመጀመሪያው ታማሚ በተገኘ ሁለት ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ ትልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ድግስ በሚሌኒየም አዳራሽ ማሰናዳቱ ነው። ይኸው ቀጥሎ፣ እስከ ትላንት ወዲያ ድረስ በርካታ የገዢው ፓርቲ ስብሰባዎች በየክልሉ ሲካሔዱ ነበር። መንግሥት በአንድ በኩል እየመከረ፥ በሌላ በኩል ምክሩን ሲያፈርስ የተመለከቱ ቢዘናጉ የሚገርም አይደለም። ብዙዎች እየተዘናጉ ነው። ገዢው ፓርቲ ገቢ ማሰባሰቢያውን ባደረገ ማግስት፥ ጭራሽ በወረረሽኙ ይበልጥ ተጠቂ የሆኑትን አረጋውያንን ለመርዳት ያሰበ ስብሰባ በዚያው ሚሊዬኒየም አዳራሽ ተካሔደ። ልብ በሉ፣ ጃፓናዊው የቫይረሱ ተጠቂ ከውጪ ሲመጣ አይደለም በበሽታው መያዙን ያረጋገጠው። ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅሎ ከሰነበተ በኋላ ምልክቶቹን ሲያይ ነው ሔዶ የተመረመረው። ለዚህ ነው እነዚህ ሁሉ ስብሰባዎች መሠረዝ የነበረባቸው። በማዘናጊያ ላይ ማዘናጊያ… ድህነት ብዙዎች በጤና ባለሙያዎች የሚመከረውን ሁሉ መተግበር እንዳይችሉ አድርጓቸዋል። ቶሎ ቶሎ መታጠቢያ ውኀ፣ የእጅ ሳሙና እንደልብ የማይገኝበት አገር ነው። ርቀትን ለመጠበቅ ከትራንስፖርት አገልግሎት እስከ መኖሪያ ቤቶች ሰዎች በሰው ላይ ተዛዝለው ነው የሚኖሩት። መኝታ ቤት የመለየት "ቅንጦት" ከጠቅላላው ሕዝብ አንፃር የጥቂቶች ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ የመንግሥት ቸልተኝነት ተጨምሮበታል። ውሳኔዎችን እስካሁንም እየተላለፉ ያሉት ከረፈደ በኋላ በብዙ ግፊት ነው። ጎረቤት ኬንያ በቫይረሱ የተያዘ ሰው አገሯ መኖሩን የተረዳችው ከኢትዮጵያ እኩል ቢሆንም፥ መንግሥታዊ ውሳኔ የሚፈልገው ጉዳይ ላይ ግን ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት። በነዚህ ሁሉ ማዘናጊያዎች ላይ የሐሰት መረጃዎች ተጨምረው ሰንብተዋል። የመጀመሪያው የሐሰት መረጃ "ኮሮና ቫይረስ ጥቁሮችን አይይዝም" የሚለው ነፋስ አመጣሽ ውሸት ነው። ሌላው በሃይማኖት አባቶች ሥም የተሰራጨ የውሸት መድኃኒት ጥቆማ ነው። ባለፈው ሳምንት ኮቪድ19 በነጭ ሽንኩርትና ፌጦ ይድናል የሚለውን ወሬ ሰምተው ያመኑ ሰዎች ጥንቃቄ ከማድረግ በእጅጉ ተዘናግተው ነበር። በሌላ በኩል ሙቀት አገር ቫይረሱ አይሰራጭም የሚለው ያልተረጋገጠ ወሬም ኢትዮጵያ ውስጥ አይስፋፋም የሚል የሐሰት መተማመኛ ፈጥሮ ሰንብቷል። እነዚህ ሁሉ ሐሰተኛ መተማመኛዎች ግን ከወር በኋላ የሚኖሩ አይመስለኝም። ከጣልያን የሚወጡ አብዛኛዎቹ መልዕክቶች የሚያሳዩት እንደኛው ተዘናግተው እንደነበር ነው። አሁን ጣልያን ቫይረሱ ከተነሳበት አገር የበለጠ ዜጎች የሞቱባት አገር ሆናለች። በዚህም መላ አገሪቱ ውስጥ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ አግዳለች። የታማሚው ቁጥር ስለበዛ የመዳን ተስፋ ያላቸውን ብቻ እየመረጠች እያከመች ነው። ጣልያን ብቻዋን አይደለችም። በመላው ዓለም በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው ያለው። … አስቀድሞ መጠንቀቅ የተፈጠሩትን የሐሰተኛ መረጃዎች ሰዎች በቀላሉ ያመኑት በፍርሐታቸው ተገፍተው ይመስለኛል። ማንም ምንም ከዚህ ወረርሽኝ አያድነንም በሚል ፍርሐት ነግሧል። ሁላችንም ከፈተናው መክበድ አንፃር ልባችንን በተለያዩ ምኞቶች እንደልላለን፤ ሁላችንም በሌላው ዓለም የሆነው በእኛ የሚሆን አይመስለንም። ሆኖም ከፍርሐትም፣ ከከንቱ ምኞትም ይልቅ መጠንቀቅ የተሻለ መፍትሔ ነው። እስካሁን በኢትዮጵያ የተደረጉት ምርመራዎች አራት መቶ አይሞሉም። ደቡብ ኮሪያ በቀን ውስጥ ከ200 ሺሕ በላይ ምርመራ በማድረግ፣ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን በጥንቃቄ በመፈለግ እና ሌሎቹንም የመከላከያ ዘዴዎች በመተግበር ስርጭቱን ሞዴል ሊባል በሚችል አሠራር እየተቆጣጠረች ትገኛለች። ኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያን ያክል ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ እንደሌላት ግልጽ ነው፤ ችግሩ ግን ያላትን አቅም ያክል እየሞከረች አለመሆኑ ነው። በቂ ምርመራ የለም። ስብሰባዎች አሁንም እየተካሔዱ ነው። ቤተ እምነቶች ውስጥ ዛሬም ግፊያዎች አሉ። ሌላው ቀርቶ የንፅሕና መጠበቂያ ሸቀጦችን ለመግዛት ሰዎች በሰው ላይ ተደራርበው ነው የሚሰለፉት። ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅን በተመለከተ እየተሰጡ ያሉ ሰበብ አስባቦች በሙሉ ወደፊት ዋጋ አላቸው። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በወረርሽኞች በተፈተነችባቸው አጋጣሚ ሟቾች ቀባሪ ያጡበት ጊዜ አለ። ክፉ ቀን ሲመጣ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያስታውሰው የለም። ወረርሽኙ እስካሁን ሕዝቡ ውስጥ ያልተስተዋለው አንድም በርካታ ምርመራዎች ስላልተደረጉ ነው። አልያም ደግሞ ብዙኀኑ ወጣት በመሆናቸው አፍነውት ለተወሰነ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። አረጋውያን ጋር የደረሰ ዕለት ግን ማቆሚያ የለውም። እውነቱን ለመናገር አሁንም ቢሆን በቫይረሱ ስርጭት እየደረሰ ስላለው ጉዳት ማንም በቂ መረጃ የለውም። የሆነው ሆኖ እጅግ ከረፈደ በኋላ ከመፀፀት አሁንም ሥር ነቀል እርምጃ ለመውሰድ ጊዜ አለ። በፍቃዱ ኃይሉ በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሐፊውን እንጂ የዶይቸ ቬለን አቋም አያንጸባርቅም።