September 28, 2020

ኡጋንዳ ተማሪዎቿን ከቻይና ለማስወጣት ገንዘብ የለኝም አለች

February 14, 1:32 pm | @BBC Amharic


ቁጥራቸው 105 ይሆናሉ የተባሉት ኡጋንዳዊያን ተማሪዎችን አውሮፕላን ተከራይቶ ከዉሃን ለማስወጣት ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ በመሆኑ አዳጋች መሆኑን መንግሥት ገልጿል። ነገር ግን ተማሪዎቹ የመዒኣስፈልጋቸውን ነገሮች እንዲያሟሉ የሚያግዝ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተጠቅሷል። በኡጋንዳ ፓርላማ ውስጥ በተካሄደ ክርክር ላይ እንደተናሳው በአሁኑ ጊዜ ተማሪዎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዕቅድ የለም። ይህም ለሳምንታት በሰቆቃና በበሽታው የመያዝ ስጋት ውስጥ ለቆዩት ተማሪዎች አሳዛኝ ውሳኔ ነው ተብሏል። የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ጄን ሩት አቼንግ ትናንት ለፓርላማው እንደገለጹት ኡጋንዳ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዕውቀትም ሆነ የተለየ ተቋም የላትም። በተጨማሪም ሚኒስትሯ ውሃን ውስጥ ለሚገኙት ለተማሪዎቹ መደገፊያ የሚሆን 61 ሺህ ዶላር በስልካቸው በኩል እንደሚላክላቸው የተናገሩ ቢሆንም እያንዳንዱ ተማሪ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚደርሰው ግልጽ አይደለም። ከተማሪዎቹ መካከልም የተወሰኑት ገንዘብ፣ ምግብና የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ ጭንብል እንዳለቀባቸው በመግለጽ እያማረሩ ነው። ተማሪዎቹ እራሳቸው ከዉሃን እንዲወጡ እንዲደረግ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ከቻይና ወደ ኡጋንዳ ትናንት ሐሙስ የገቡ ከ260 በላይ የሚሆኑ ኡጋንዳዊያንና ቻይናዊያን ለሁለት ሳምንት እራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች አግልለው እንዲቆዩ መንግሥት ጠይቋል። ባለፈው ሳምንት በኢንቴቤ አየር ማረፊያ በኩል ከቻይና የገቡ 100 የሚሆኑ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጓል። ተገቢው ምርመራ ሳይደረግ ሰዎች ወደ አጋንዳ እየገቡ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግሥት የወሰደው ይህ እርምጃ በሽታውን ለመቆጣጠር ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል በሚል ጥያቄ እየቀረበ ነው።