April 7, 2020

ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው

January 24, 6:42 pm | @DW


ይሻራሉ ተብለው ከሚታሰቡት የሕወሓት አባሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) አንዱ ናቸዉ። እርምጃዉ ሕወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥቱ ገሸሽ የማድረጊያ ዘመቻ ነው ተብሎ ተገምቷል። ሕወሓትም በመግለጫው “የሕወሓት አመራሮችና አባላት በመሆናቸው ብቻ ከፌዴራል መንግሥትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የኃላፊነት ቦታዎች እንዲነሱ እየተደረገ ነው” በሚል አቤቱታ፣ መግለጫ እና ማስጠንቀቂያ መሰል መልዕክት አስተላልፏል። ሕወሓት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የነበረ ድርጅት ነው። የአሁኑን መንግሥታዊ ስርዓት በዋና ተዋናይነት የቀረፀ አካል እንደመሆኑ፥ የጠባቂነት ስሜትም አለው። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዕለት ዕለት አቅመ ቢስነቱ እየተስተዋለ ነው። ገንብቼዋለሁ የሚለውን ስርዓት ሊያድን ቀርቶ የራሱን ሕልውና እንኳን ማስጠበቅ ያቃተው ይመስላል። ስለሆነም ያልሞት ባይ ተጋዳይነት ጫፍ ላይ ደርሷል። ቀድሞ ተቃዋሚዎች በመግለጫዎቻቸው “ያስጨንቁት” የነበረው ይሄ ኃያል ቡድን፥ ዛሬ ግን መግለጫ ከማውጣት በቀር አቅም የሌለው ቡድን እየመሰለ ነው። በርግጥ በዚህኛው መግለጫው የሕወሓት አመራር እና አባላትን ከሥልጣን የማንሳቱ ድርጊት ካልታረመ “ይህንን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ ኀላፊነት የሚወስደው ይህ ሕገ ወጥ ተግባር እየፈፀመ ያለው አካል መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል” በሚል ማስፈራሪያ ነው የደመደመው። የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ይሆን? ለመሆኑ የሹም ሽረቱ “ጥፋት” የቱ ላይ ነው? አዲሱ የትግራይ ብሔርተኝነት ትርክት በቅርቡ ከአንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የትግራይ ብሔርተኛ ጋር በወቅቱ ሁኔታ ላይ እየተነጋገርኩ ነበር። ይህ ብሔርተኛ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተቀየረ የመጣውን ትርክት ሊያስረዳኝ እየሞከረ ነበር። ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥቱ መገፋቱን “ኢትዮጵያን ከመፈራረስ አደጋ በማዳን በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የትግራይ ሕዝብ ላደረገው ውለታ” ምላሹ አመድ አፋሽነት እንደሆነ አድርገው እንደሚረዱት ሲያብራራ ነበር። እንደርሱ አባባል፣ የትግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያ ላይ ዕውቀት እና ሀብታቸውን መሐል አገር ላይ ማፍሰሳቸውን አቁመው ትግራይ ላይ ብቻ ማፍሰስ አለባቸው የሚል ስሜት አለ። ለዚህ ሲባል “ትግራይ መገንጠል ካለባትም ትገንጠል” ባይ ነው - ይህ ብሔርተኛ። የዚህ ብሔርተኛ አቋምና አረዳድ የምን ያህሎች የትግራይ ተወላጆች አቋም እንደሆነ ለመደምደም ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። ነገር ግን ትርክቱ ከየትም አልመጣም። ሕወሓት በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ ያለውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከተነፈገ በኋላ የትግራይን ሕዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ ሲጠቀምበት የነበረው ትርክት ነው። የሰሞኑ ሹም ሽረት ቀድሞም ሆድ ለባሰው ሕወሓት ተጨማሪ የብስጭት መንስኤ ነው። የብልፅግና ካቢኔ ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ ሳይወዳደር ገዢ ፓርቲ ለመሆን የበቃ ድርጅት ነው። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 56 በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ወይም ጣምራ ድርጅቶች መንግሥት እንደሚመሠርት/ቱ ይናገራል። ኢሕአዴግ በዚህ መሠረት የአራት ፓርቲዎች ግንባር ሆኖ ያገኘውን ሥልጣን ብልፅግና ሦስቱን ድርጅቶች በማክሰም እና በማዋሐድ ቀምቶታል ማለት ይቻላል። ይህንን ሕወሓት “ሕገ ወጥ” ድርጊት እያለ እየተቃወመው ነው። እንደ ምክንያት የሚጠቅሰውም ‘ዜጎች ድምፅ የሰጡት ለኢሕአዴግ ፖሊሲ ነው አሁን መንግሥትን የሚመራው ሌላ ርዕዮት እና ፖሊሲ ያለው ድርጅት ነው’ የሚል ነው። ይህንን መከራከሪያ ይዞ ነው አባሎቼ ሹመት መነፈግ የለባቸውም የሚለው። የብልፅግና ፓርቲ አካሔድም ግልጽ ይመስላል። የሕወሓት አመራር የሆኑትን ሚኒስትር ካነሳ በኋላ ሌላኛውን የትግራይ ተወላጅ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አድርጎ በመሾም መልዕክት አስተላልፏል። አብርሃም በላይ ከሕወሓት ይልቅ ለብልፅግና ፓርቲ የወገነ አስተያየት እያቀረቡ እንደነበር ተስተውሏል። መልዕክቱ “ፀቤ ከሕወሓት እንጂ ከትግራይ ተወላጆች አይደለም” የሚል ነው። የሚኒስትሮች ካቢኔ ከዚህ በፊት በአራቱ የግምባሩ አባላት እና አጋር ፓርቲዎች ድርድር የሚወሰን ሲሆን፥ አሁን ደግሞ በዚያው ልማድ በብልፅግና ፓርቲ አባላት ድርድር እየተወሰነ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል። ስለዚህ ጉዳይ አስተያየቱን የጠየቅኩት አንድ ሰው፣ ‘ከብልፅግና ፓርቲ አንፃር ሕወሓት ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ተቃርኖ እየሠራ ባለበት በዚህ ጊዜ የሚኒስትሮች ካቢኔ አባል አድርጎ ማስቀጠል በራስ ላይ እንደማሴር ነው’ ብሎ እንደሚያምን ገልጾልኛል። ይህ በእንዲህ እያለ፣ ሆድ የባሰው ሕወሓት “ይህንን ተከትሎ በሚፈጠረው ሁኔታ ላይ” ብሎ ያለው ምኑን ይሆን? ቀደም ብለን የጠቀስነው እና እየተለወጠ የመጣው የትግራይ ብሔርተኝነት ትርክት ምናልባት ምልክት ይሰጠናል። ሕወሓት ማዕከላዊ መንግሥት ውስጥ የቀረኝን ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ ካጣሁ ፌዴሬሽኑ ውስጥ የምቆይበት ምክንያት የለኝም የሚል የፖለቲካ ካርድ ሊመዝ ይችላል። “ለዚህም ኀላፊነቱን የሚወስደው” ብልፅግና ፓርቲ ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ ነው “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው” ብሎ መተረት አስፈላጊ የሚሆነው። የብልፅግና ፓርቲ ወደ ሥልጣን ሲመጣ እንደ ቅቡልነት ማግኛ የተጠቀመበት የሕወሓትን ገመና እንደመሆኑ አብሮ ለመሥራት አለመፈለጉን መረዳት ይቻላል። ሕወሓትም ከኀያልነት ወደ ደካማ ተቃዋሚነት መቀየሩን በቀላሉ አምኖ መቀበል አለመቻሉን መረዳት ይቻላል። ነገር ግን የሁለቱም ፓርቲዎች መሪዎች የግል ኩራትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚል አገራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል እርምጃ ሲወስዱ እያዩ መረዳት የሚቻል አይመስለኝም። ከዚህ የበለጠ ሳይረፍድባቸው ቁጭ ብለው በመደራደር ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሔ ቢያበጁ መልካም ነው። በፍቃዱ ኃይሉ ነጋሽ መሐመድ